አንድን ነገር ወይም ጉዳይ ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርገው በአመዛኙ የአንተ አተያይ ነው። የአንተ አመለካለት የበሰለ ከሆነ ሌሎች መጥፎ ብለው ከሚያስቡት ክስተት አንተ እጂግ በጣም ጥሩ ነገር ልታይ ትችላለህ ። የበቁ ሰዎች ብዙ ጊዜ አመለካከታችን ላይ እንድንሰራ ወይም እንድናሻሽል የሚመክሩን ለዚሁ ነው። ችግሩ የእራሳችን ክፍተት እንዲሁ በቀላሉ አይታየንም እንጂ።
አሁን እንደዚህ የዘነጠው በተለምዶ ኤርጌንዶ ብለን የምንጠራው ክፍት ጫማ አመጣጥ ለአመለካከታችን ልዩነት ጥሩ ማስረጃ ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው ( ካነበብሁት) ። ቀደም ባለ ጊዜ ሁለት አመሪካውያን ለጉብኝት ወደ ህንድ ሃገር ይሄዳሉ። ሁለቱ ጎብኝዎች ህንድ ሲደርሱ የተመለከቱትን ማመን አልቻሉም ነበር። እጂግ በጣም ብዙ ሰዎች በባዶ እግራቸው ይሄዱ ስለነበር በጣም ተገረሙ። እነሱ ከመጡበት ሃገር በባዶ እግር ስለማይኬድ ሁለቱም እጂግ ተገርመው ነበር።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ጉዳዩን በአንድ ዓይነት አልተመለከቱትም። ከሁለቱ አንደኛው በጣም ደንግጦ ስለነበርና የሰዎች በባዶ እግራቸው መጓዝ በጣም አስፈርቶት ስለነበር በመጣበት አውሮፕላን ተመልሶ ወደ ሃገሩ ሲጓዝ፤ ሁለተኛው አመሪካዊ ደግሞ የሰዎች በባዶ እግራቸው መጓዝ ጫማ ለመነገድ በጣም ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተገንዝቦ እዛው በሄደበት ቅጽበት ቀላልና እርካሽ የሆነ የጫም ዲዛይን በመስራትናት ከአምራች ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ቀላልና እርካሽ የሆነ ኢርጌንዶ ጫማ በማምረትና በመሸጥ የእራሱን ገቢ ሲያሻሽል የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን የጫማ ችግር መቅረፍ ችሏል ይባላል።
ስለሆነም ፊትለፊትህ ያለውን ነገር ወይም ጉዳይ እንደእድል መቁጠርና የተሻለ ተግባር እንዲከውን ማድረግ የአንተ ምርጫ ነው። ግማሽ ባዶ ብርጭቆውን ከማየት ግማሽ ውሃ የያዘውን ብርጭቆ በማሰብ ሙሉ ብርጭቆ ውሃ እንዲሆን መትጋት የተሳሻለውና አዋጩ አማራጭ መሆኑን ተገንዝበህ መልካሙን ወይም የተሻለውን አማራጭ ማሰብና መተግበር ያዋጣሃል።
አመለካከትህ ሁሉ ነገርህ መሆኑን ተገንዘብና ለመቀየር ወይም ለማሻሻል በየቀኑ ጥረት አድርግ። ብዙ የስኬትህ ወሳኝ ቁም ነገሮች አንተው ጋር ናቸውና ያሉት ።
Discussion about this post
No posts